የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ኮሙኒኬሽንና ሥነ ጽሑፍ መምሪያ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጥንታዊና ረጅም ታሪክ ካላቸው የአገልግሎት መምሪያዎች አንዱ ነው። ለብዙ ዓመታት በወንጌል ስርጭት፣ በክርስቲያናዊ ትምህርት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ሰነድ አያያዝና በሕትመት አገልግሎት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል።
መምሪያው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ መጻሕፍትን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ የሚያስቀምጡ ሕትመቶችን በማዘጋጀት ለአማኞችና ለሕብረተሰቡ ሲያቀርብ ቆይቷል። እነዚህ ሕትመቶች የወንጌል መልእክትን ከማሰራጨት ባሻገር የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ፣ እሴቶችና አገልግሎቶች ለትውልድ በማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ መምሪያው የራሱን ማተሚያ ቤት በማቋቋም የቤተ ክርስቲያኒቱን የውስጥ የሕትመት ፍላጎቶች በማሟላት እና የተለያዩ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ ሪፖርቶችና ሌሎች ሕትመቶችን በሙያዊ ደረጃ በማዘጋጀት አገልግሎት ሰጥቷል። እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን የማኅተም ሥራዎች በኃላፊነት በማከናወን የተቋሙን ኦፊሴላዊ ሰነዶች ተአማኒነት ለማረጋገጥ ያገለግላል።
በአሁኑ ጊዜም መምሪያው ከባህላዊ የሕትመት አገልግሎቶች በተጨማሪ የዲጂታል ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በማስፋፋት የቤተ ክርስቲያኒቱን መረጃዎች፣ ዜናዎች፣ መግለጫዎች፣ ሥነ ጽሑፎችና ሌሎች ይዘቶች በዘመናዊ የመገናኛ መንገዶች ለአማኞችና ለሕብረተሰቡ እንዲደርሱ ይሠራል። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ሰነዶች፣ ፎቶግራፎችና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች በመሰብሰብና በማደራጀት የታሪክ ቅርሷን ለቀጣይ ትውልድ ለማስጠበቅ ይተጋል።